በሰ/ሸዋ ዞን የሚዳ ወረሞ ወረዳ የ2018 የትምህርት ዘመን በሶስት ትምህርት ቤቶች የፖይለት ምዝገባ ነሐሴ 19/2017 ዓ.ም ማስጀመሩን የወረዳው ትምህርት ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
የወረዳው ትምህርት ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ንጉስ አጥሌ እንደተናገሩት ከአጋርና ባለድርሻ አካላት ጋር የተማሪ ምዝገባ ንቅናቄ ለማካሄድ በተግባባነው ልክ ቅድመ ዝግጅታችንን አጠናቀን ወደ ሥራ በመግባት ዛሬ ላይ በተመረጡ ሶስት ትምህርት ቤቶች የፖይለት ምዝገባ አስጀምረናል ብለዋል።
በ2018 ዓ.ም በወረዳው በሁሉም ቀበሌዎችቅድመ አንደኛ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 39ሺህ 437 ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር ማቀዱን የገለፁት አቶ ንጉስ የነገ ሃገር ተረካቢ ትውልድ ለመገንባት በሚደረገው ሂደት ሁሉም የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበት አሳስበዉ ለትምህርት የደረሱ ህጻናት ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዳይሆኑ የተማሪ ወላጆች፣ የቀበሌ አደረጃጆቶች፣ የቀበሌ አመራሮችና መላው ማህበረሰባችን በርብርብ ተማሪዎችን ማስመዝገብ ይኖርበታል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
አቶ ንጉስ አክለዉም የፖይለት ምዝገባው በስኬት አንዲጠናቀቅ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀትና የተሟላ ቅድመ ዝግጅት በመደረጉ ተማሪዎች በነቂስ ወጥተው መመዝገብ መቻላቸውን ተናግረዋል።
የወረዳዉ ብልጽግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ አየናቸዉ ጌታሁን የገጠመን የፀጥታ ችግር በትምህርት ዘርፉና በነገ ሀገር ተረካቢ ልጆቻችን ላይ ትልቅ ጠባሳን አሳርፏል ነገር ግን በችግር ውስጥም ሆኖ መስራት እና ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ያየንበት ወቅት ነው፤የሚያጋጥሙንን ችግሮች በመጋፈጥ ትውልድ እንዲቀጥል የቅንጅት ስራ በመስራት የትምህርት ስራችን የተቃና እንዲሆን ልናደርግ ይገባል ብለዋል።
ወ/ሮ አየናቸዉ በተጨማሪም የ2018 ዓ.ም ዋናው ግባችን ተማሪዎችን ከመመዝገብ ባለፍ አመቱን ሙሉ ከትምህርት ገበታ ውጪ እንዳይሆኑ ይዞ መዝለቅ ነው ብለው በወረዳችን የመጣውን አንፃራዊ ሰላም በመጠቀም የትምህርት ዘርፉን ማነቃቃት እንደሚገባ ገልጸዋል።
ባለፉት አመታት ወረዳው በገጠመው የፀጥታ ችግር ምክንያት በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ሆነው መክረማቸውን የገለፁት የወረዳዉ ብልጽግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት ፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አበበ ገለታዉ በ2018 ዓ.ም የትምህርት ዘመን አንድም ተማሪ ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆን የለበትም ፤ ትምህርት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማታችንን ለማፋጠንና የአመለካከትና የአስተሳሰብ አድማስን በማስፋት የምርምርና የፈጠራ ችሎታን በማዳበር፣ የሀገርን እድገት ለማሳደግ ቁልፍ መሳሪያ ነዉ ይህ ተግባር እንዲሳካ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡



